የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሩን ፓርቲ የአገሪቱን ፓርላማ 90 በመቶ መቀመጫን አሸነፈ

የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ፓርቲ የአገሪቱን ፓርላማ 90 በመቶ መቀመጫን አሸነፈ ፡፡              

የፓርቲያቸው አብላጫ ወንበር መያዝ ለፕሬዝደንቱ  የመንግሥት ምሥረታና መዋቅራዊ ለውጥ ያግዛል ተብሏል ፡፡ 

አደሲ ተመራጭ የፈረንሳዩ ወጣቱ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ጂን ሚኬል ፌሬድሪክ ማክሩን ዘንድሮ እጅጉን እድለኛ እንደሆኑ  እየተነገረ ይገኛል ።

በወጣቱ አብዮተኛ የሚመራው የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ ያለው ፓርቲያቸውም እንደሳቸው የድል ዓመቱን እያጣጣመ ይገኛል ይላሉ ለሮይተርስ የሚጽፉት ኢንግሪድ ሜላንደር እና ሚኬል ሮዝ፡፡

ፈረንሳያውያን ፕሬዝዳንቱን ወደዋቸዋል፣ የፕሬዝደንቱን ፖሊሲም እንዲሁ፤ ለዚህም ይመስላል የናሽናል ፍሮንት ፓርቲዋንና በፖለቲካ በሳል የተባለችውን ማሪን ለ ፔንን ወደ ጎን ትተው ስልጣን መንበሩን ለወጣቱ ሰው ያስረከቡት፡፡

የፕሬዚዳንቱ የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ለውጥን በፓሪስ እተገብራለሁ ብለው መነሳታቸውን ተከትሎ፤ የፈረንሳይ ኢኮኖሚ በሀያላኑ እጅ የተያዘውን በትር ይጨብጣል የሚል ዝንባሌ አላቸው፡፡

አሁን 577 መቀመጫ ያለውን የአገሬውን ፓርላማ በ445 ወንበር ተቆጣጥረውታል፡፡ ይህም እቅዳቸውን ለማሳካት ሰፊ መንገድ ከፍቶላቸዋል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡

የሶሻሊስት እና ወግ አጥባቂዎቹ ላለፉት አስርት ዓመታት እየተፈራቁ አገሪቱን መርተዋታል፡፡

ሰውየው ዘጠና በመቶውን የመራጮችን ድምጽ ሲያገኙ ከአጠቃላዩ ምርጫ 31 በመቶ ድርሻ ነው ያላቸው፡፡ ይህ ደግሞ ጎልተው የማይወጡ ተጽእኖም መፍጠር የማይችሉ በርካታ ፓርቲዎች ምክር ቤቱን እንዲቀላቀሉ አስችሏል ነው የተባለው፡፡

ይህ በአክራዎቹ ዘንድ ተቀባይነትን አላስገኘም፡፡ ፈረንሳይ አሁን ገና ወደ ውድቀት ጎዳና ማምራት ጀምራለች ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በፕሬዝደንቱ የሥልጣን ዘመን የፓሪስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መላው ዓለምን እንደሚያዳርስ የባለፈውን የማሊ ጉብኝት ማንሳት በቂ ነው፤ አገሪቱም ከሃያላን ተርታ የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የምትገሰግስ መሆኗንም የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ያስረዳል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም በአውሮፓ ህብረትም ፈረንሳይ ፈላጭ ቆራጭ ትሆናለች የሚሉ አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የፕሬዝደንቱ ፓርቲ አብላጫ ወንበር መያዝ ለእቅዳቸው ስኬት ይረዳቸዋል ተብሏል፡፡