የኬንያ አየር መንገድን ከገጠመው ኪሣራ ለማዳን የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ

የኬንያ አየር መንገድ  ከገጠመው ኪሳራ ማገገም ባለመቻሉ የመንግስት ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ፡፡

የአየር መንገዱ የብድር ዕዳ ከ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መብለጡ ሲገለፅ ፤ መንግስት 243 ሚሊየን ዶላር ገንዘብን ወደ ንብረት ቀይሮ እንደሚያበድር ጠቅሷል፡፡

የኬንያን አየር መንገድ 29 በመቶ የአገሬው መንግስት ፤ 26 በመቶ የሚሆነውን የፈረንሳዩ አየር መንገድ ኬ. ኤል. ኤም. በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ተቆናጥጠዋል፡፡

አገሪቱ በቀዳሚነት የምትጠቀስበትን ቱሪዝም እንዲደግፍ የቤት ስራ የተሰጠው አየር መንገዱ በሁለት እግሩ መቆም አቅቶታል ነው የተባለው፡፡

መንግስት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የ243 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ብድር ሊሰጥ እንደሆነ ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡

 ነገር ግን የሚደረገው የብድር ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጥ ሳይሆን በንብረት መልክ ተቀይሮ እንደሚሆን ጠቅሷል፡፡

መንግስት ይህን አሰራር ያመጣው አየር መንገዱ እስካሁን በተደረገለት የገንዘብ ድጋፍ እና ብድር ሊያገግም ባመቻሉ እና ይበልጥ የኪሳራውን መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ድርጅቱ ያቀደውን ተጨማሪ የቦይንግ አውሮፕላኖች ግዢ እና የማስፋፊያ ስራ ማገዝ ብቸኛ የመደገፊያ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ተቋሙን መልሶ ለማቋቋም ይረዳል የተባለው የብድር ድጋፍ በዚህ ወር በምክር ቤቱ ይሁንታ ያገኛል ተብሏል፡፡ ድጋፉም ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የተነገረው፡፡

አየር መንገዱ 750 ሚሊየን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ከረጂ ተቋማት የሚያገኝ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ኬንያ የቱሪዝም ዘርፉን እንዲደግፍ በያዘችው እቅድ መሰረት በቢሊየን ሺሊንግ ለአየር መንገዱ በቅርቡ የእድሳት እና የማስፋፊያ እንዲሁም የአዳዲስ አየር መንገዶች ግንባታ አከናውናለች፡፡

በአሁኑ ድጋፍም አየር መንገዱ ካለበት የሁለት ቢሊየን በላይ የብድር እዳ ቢያንስ ግማሽ ያህሉን እንድትቀንስ የሚያስችላት የንብረት ግዢ እንደሚከናወን ነው የተገለፀው፡፡

የኬንያ አየር መንገድ በቀን ከ12 ሺህ በላይ መንገደኞችን እንደሚያስተናግድ አስታውሶ የዘገበው አፍሪካ ቢዝነስ ሴንትራል ነው፡፡