ደቡብ ሱዳን በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንደማትቀበል አስታወቀች

አሜሪካ በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንደማትቀበል ደቡብ ሱዳን አስታውቃለች፡፡

የአሜሪካ ግምጃ ቤት በጥቁር መዝገብ ውስጥ ካካተታቸው መካከል፤ የሱዳን መከላከያ ኃይል የሎጂስቲክስ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ማሌክ ሪዩቤን ሪያክ ሬንጉ፣ በግንቦት ወር ሥልጣናቸውን ያስረከቡት የቀድሞ የሃገሪቱ የጦር  ኃይሉ ኃላፊ ፖል ማሎንግ እና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ሚካኤል ማኩይ ይገኙበታል፡፡ 

አሜሪካ ወንጀለኞች ናቸው ብላ በጥቁር መዝገብ ካስቀመጠቻቸው የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዱ ፤ የመከላከያ ኃይል የሎጂስቲክስ ምክትል ሃላፊ የሆኑት ማሌክ ሪያክ በመጀመሪያዎቹ የግጭት ዓመታት ላይ በጦር መሳሪያዎች ግዢ ላይ ማጭበርበር ፈፅመዋል፡፡

በተጨማሪም የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሁሉም የመዋዕለ ንዋይ ኢንቨስትመንት፣ የኤሌክትሮኒክስና ሚድያ ህትመት እና ማክ ዓለምአቀፍ አገልግሎት የተባለውና በመከላከያ ኃይል የሎጂስሰቲክስ ምክትል ኃላፊ በሆኑት ማሌክ ባለቤትነት የሚተዳደሩትን ድርጅቶች በሙሉ በጥቁር መዝገብ ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡

አሜሪካ በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በማነሳሳት እጃቸው አለበት ያለቻቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ፥ የደቡብ ሱዳን መንግስት አሜሪካ  በሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንደምትቃወም አስታውቃለች፡፡

አሜሪካ በዜጎች ላይ የጣለችውን የማዕቀብ ውሳኔን እንደገና ማጤን አለባት ምክንያቱም በሃገራችን ሰላም ለማስፈን የምናደረገውን ጥረት ያስተጓጉላል  ብላል የደቡብ ሱዳን መንግሥት ፡፡

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ማዊን ማኮል፥ "ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምንፈልጋቸው ነገሮች የሞራል እና የገንዘብ ድጋፎች እንጂ ማዕቀብ መጣል አይደለም፡፡

የአሜሪካ መንግስት ያስቀመጠው እገዳም የሀገራትን ግንኙነት የሚያሻክርና ጥቅም የሌለው ነው፡፡ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አራተኛ ዓመቱን የስቆጠረው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች ለሞት ሲጋለጡ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ ለስደት መዳረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡