በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የነዳጅ ፍላጎት እንደሚያድግ ተገለጸ

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ፍላጎት ከተጠበቀው በላይ ዕድገት ያሳያል  ተባለ፡፡

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በ2017 የዓለም  የነዳጅ  ፍላጎትን መሠረት በማድረግ  በሠራው  ትንተና ወቅት  ነው  የዓለም  የነዳጅ  ፍላጎት  ዕድገት  እንደሚያሳይ የተጠቆመው ፡፡

በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ ቆይቷል፡፡

በመሆኑም ምጣኔ ሃብታቸውን ነዳጅ ላይ ያደረጉ አገሮች ሌሎች የምጣኔ ሃብት አማራጮችን እንዲጠቀሙም አስገድዷቸዋል፡፡

በተለይም እንደ ናይጀሪያ ያሉ አገራት የነዳጅ አቅርቦታቸውን በመቀነስ በሌሎች ስራዎችም እንዲሰማሩ አለም አቀፉ የነዳጅ ላኪ ሃገራት ማህበር ኦፔክ የብድር ድጋፍ እንደሚያደርግም መናገሩ ይታወሳል፡፡

የነዳጅ አቅራቢ ሃገራትም አቅርቦታቸውን በመቀነስ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር አድርገዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ የነዳጅ ፍላጎት አሁን ካለበት በተወሰነ መልኩ እንደሚጨምር የተነበየ ሲሆን የ2017 የዕድገት ግምቱን በከለሰበት ወቅት ግን አቅርቦት እና ፍላጎት ቀድሞ ከተተነበየው በቀን የ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በርሚል ወይም የ 1ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ይፋ ያደረገው፡፡

በዚህም መሰረት በቀን ቀድሞ ከነበረው የፍላጎት መጠን የ2 ነጥብ 3 ሚልየን በርሚል ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ማለት በፈረንጆቹ ሁለተኛው ሩብ ዓመት የ 2ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ያሳያል እንደ ማለት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ የነዳጅ ኢንዱስትሪ እና የገበያ ክፍል ኃላፊ ኒል አትኪንሰን አሁን ላይ ያለው በጣም ጠንካራ ፍላጎት ሚዛናዊ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ የነዳጅ ገበያ የሚያበረታ ነው ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ ነሐሴ ወር ላይ ቀድሞ ከነበረው የነዳጅ አቅርቦት በቀን 720 ሺህ በርሚል ቀንሷል፡፡

እሮብ እለትም አንድ በርሜል ነዳጅ በ54 ነጥብ 39 ዶላር ሲሸጥ ውሏል፡፡ ( ምንጭ: ሲኤን ኤን)