ግብጽ ሰላሳ ሺህ ተወንጫፊ ሮኬቶችን ከሰሜን ኮሪያ ለመግዛት ከስምምነት ላይ ደርሳለች ተባለ

ግብፅ ሰላሳ ሺህ ተወንጫፊ ሮኮቶችን ከኮሪያ በድብቅ ለመግዛት  ከስምምነት ደርሳለች ተባለ፡፡

አገሪቱ የጦር መሣሪያ ግዢውን በተመለከተ የወጣው መረጃ የሀሰት ውንጀላ ነው ስትል፤ ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ደግሞ ካይሮ እያጭበረበረች ነው ብለዋል፡፡

አሜሪካ እና ግብፅ ለዓመታት የቆየው ወዳጅነታቸው ካይሮ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ባላት ግንኙነት ስጋት ላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡       

ዋሽንግተን በየዓመቱ ለካይሮ የምታደርገውን የጦር ድጋፍ እንዲዘገይ ማድረጓም የትራምፕ አስተዳደር ለአልሲሲ መንግስት የሠጠውን ማስጠንቀቂያ ግብፅ ከቁብ ባለመቁጠሯ ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡  

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ወር አሜሪካ ከፒዮንግያንግ ወደ ካይሮ እየተላከ ነው ያለችውን የጦር መሳሪያ የጫነ መርከብ ወደ ግብፅ የባህር ዳርቻ እንዳይደርስ የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ አገሪቱ ከፒዮንግያንግ ጋር ያላትን ምስጢራዊ ግንኙነት በማጣራት ላይ መክረሟም ነው የሚነገረው፡፡

ግብፅ በበኩሏ ለጦር መሳሪያ ግዢ ምንም አይነት ድርድር ከኪም ጆንግ ኡን ጋር አለማድረጓን ገልፃ የመንግስታቱን ድርጅት የማጣራት ሂደት ደግፋለች፡፡

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት እንደሚያሳየው በግብፅ ከሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠር አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ባለሃብት የጦር መሳሪያዎቹን በድብቅ ስለመግዛቱ ባደረገው ምርመራ እንደደረሰ ቢያስረዳም ይህ አመክንዮ ግን ለትራምፕ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡

አሜሪካ የ300 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታው እንዲዘገይ ማድረጓም ለዚህ ነው፡፡ ግብፅ በድብቅ ትገዛዋለች የተባለው 30 ሺ ተወንጫፊ ቦምብ PG-7  የሚል ስያሜ ያለውና በ1960ዎቹ የተፈበረከ የሶቪየት ህብረት ዋነኛ ትጥቅ እንደነበርም ይነገራል፡፡

ከአጠቃላዩ የጦር መሳሪያ 24 ሺ የሚሆነው ባለሙሉ ቁስ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶች ሲሆን ስድስት ሺ ያህሉ ደግሞ አውዳሚ ሮኬት እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከግብፅ ጋር እ.አ.አ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት ያስታወሰው ዘገባው በጦር መሳሪያ ሽያጭ ፒዮንግያንግ ከግለሰቦችና ቡድኖች ጋር ሳይሆን ከአገራት ጋር እንደምትነጋገርም ነው የተገለፀው፡፡

ይህም ጉዳዩን አወዛጋቢ ሲያደርገው ለአሜሪካ ጥርጣሬዋን እንድታረጋግጥ ምላሽ የሚሆናት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የተለያየ ትንትና የሚሠጡት ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ግብፅ እያጭበረበረች እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

አገሪቱ አሁንም ከሁለቱ ተፃራሪ ኃያላን ጋር እያደረገች ያለው ምስጢራዊ ግንኙነት መልሶ ለእራሷ ጦስ እንዳይሆናት ሲሉ ስጋት አዘል ትንበያ የሚሰጡም አልጠፉም፡፡    

ግብፅ ግን አሁንም ወታደራዊ አቅሟን ለማጠናከር በፍጥነት እየተጓዘች እንደሆነ ጠቁሞ የዘገበው ታይምስ ኦፍ ኢስራኤል የተሰኘው የዜና ምንጭ እና ዋሽንግተን ፖስት ናቸው፡፡