የአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሥራ አጥነትን በመቀነስ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ተገለጸ

የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ስራ አጥነትን በመቀነስ ላይ ያተኮረና የሃብት ልዩነትን በማጥበብ ላይ ማተኮር እንዳለበት ተገለፀ፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመክረው የአፍሪካ ህብረት የፋይንናስና የኢኮኖሚ ጉዳዮች 3ኛ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ የሚንስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱ በዋነኝነት ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል የአፍሪካ ህብረት በገቢ ራሱን ይችል ዘንድ አባል አገራቱ ባለፈው አመት የተስማሙበትን ከአፍሪካ ውጭ በሚያስገቧቸው እቃዎች ላይ ተጨማሪ የዜሮ ነጥብ 2 በመቶ ቀረጥ በመጣል ህብረቱን የመደገፍ እቅድ ላይ መወያየት አንዱ ነው፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ባለፉት 10 አመታት በአማካኝ 5 በመቶ እያደገ የመጣ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እድገቱ መቀነስ ጀምሯል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሥራ አጥነትንና የሃብት ልዩነቶችን ማዕከል አድርጎ የመቀጠል ክፍተትም  እንደሚታይበት  እየተካሄደ ባለው  ውይይት ተገልጿል ፡፡

አባል አገራትም የሚስተዋሉ ችግሮች በመቀነስ ላይ በማተኮር መሥራት አለባቸው ሲሉ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ቪክቶር አሪሰን አሳስበዋል፡፡

ውይይቱ የአህጉሪቱን የፋይናስና የኢኮኖሚ ችግሮች ማቅለል የሚችሉ ረቂቆችን በማዘጋጀትና በማፅደቅ አርብ ጥቅምት 17 ይጠናቀቃል፡፡