የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ኡጋንዳ ጉብኝት ሊያደረጉ ነው ተባለ

የሱዳኑ ፕሬዚዳነት ኦማር አል በሽር ኡጋንዳ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ ።  

ጉብኝቱ ከነገ አንስቶ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑም ታውቋል፡፡ ሀገራቱ በንግድ እና ኢንቨስትመንት እድል፤ በኢሚግሬሽን፤ በአየር ትራንስፖርት፤ በአህጉራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡      

ኡጋንዳና ሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማጠናከር ላይ ናቸው፡፡ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ልዑክ ከአንድ ወር በፊት በኡጋንዳ ለሁለት ቀናት ጎብኝት አድርጎ ነበር፡፡

በወቅቱ የኡጋንዳው አምባሳዳር ፓትሪክ ሙጋያ ሀገራቱ በካርቱም በተደረገው አምስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ካርቱም በነበረው ውይይት በንግድ እና ለኢንቨስትመንት እድል፤ በኢሚግሬሽን፤ በአየር ትራንስፖርት፤ በአሁጉራዊ ጉዳዮች እና በደህንነት አጀንዳዎች ዙሪያ መክረው ነበር፡፡ 

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መስከረም 2015 በሱዳን የሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱም ለትምህርት ባለሙያዎችና ለሲቪል ማህበረሰብ አካላት በምጣኔ ሃብታዊ ልማት እና የሰላም ግንባታ ችግሮች ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ 

ፕሬዝዳነት ሙሴቬኒ በታህሳስ 2016 ለሁለተኛ ጊዜ በካርቱም ተገኝተው ከፕሬዝዳንት አል በሽር ጋር የሀገራቱን ግኑኝነት የበለጠ ለማጠናከር ዳግም መክረው ነበር፡፡

ሱዳን ከኡጋንዳ የቡና ምርት 20 በመቶውን ወደ ሀገሯ የምታስገባ ሲሆን 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በማድረግ በዓለም ገበያ ትልቅ ድርሻ ያላት ሀገር ነች፡፡

ከሱዳን የደረጃዎች እና የሥነ-ልክ ባለሞያዎች የተውጣጡ ልዑካን የኡጋንዳን የቡና ልማት ኤጀንሲ ጥራት ለማረጋገጥ ከሰባት ቀናት በፊት ወደ ካምፓላ አቅንተው ነበር፡፡ በቆይታቸውም ከሚኒስትሮችና ባለድርሻ ካላት ጋር በቡና ግብይት ዙሪያ መክረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት አል በሺር በነገው እለት በሚያደርጉት ጉብኝት በንግድ ሚኒስትሮች፤ በከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከተለያየ ዘርፍ ከተዉጣጡ ልኡካን ጋር ወደ ስፍራው ያቀናሉ ነው የተባለው፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ሁለቱ ሀገራት የንግድ ፎረም እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ ኡጋንዳ ስድስተኛውን የጋራ ኮሚሽን በመጪው እኤአ በ2018 እንደምታስተናግድ ከወዲሁ ታውቋል፡፡

ፕሬዝዳንት አልበሽር  ወደ ካምፓላ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት መጠናቀቅ ተከትሎ ከኡጋናዳ አቻቸው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በጋራ መግለጫ እንደሚያወጡ ከወዲሁ የዘገበዉ ኒውስ ናዎ ነው ፡፡