የኢሲያ ፓስፊክና የደቡብ ምስራቅ ኢስያ ህብረት ተቀራርበው መሥራት አለባቸው-ፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ

የኢስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ጥምረት እና የደቡብ ምስራቅ ኢስያ አገራት ህብረት ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ሲሉ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂን ፒንግ አሳሰቡ፡፡

የተቋማቱ በጋራ መሥራት ለቃጣናው እድገት እና አገራቱ በመሠረተ ልማት እንዲበለጽጉ ያግዛቸዋል ነው ያሉት፡፡

የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂን ፒንግ ከተቋማቱ መሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ጥምረት እና በደቡብ ምስራቅ ኢስያ አገራት ህብረት እንቅስቃሴ ውስጥ አገራቸው ስለሚኖራት ሚና ተወያይተዋል፡፡

ቻይና ለቃጣናው ልማት እና እድገት በተለይም ተቋማቱ እንዲያሳኩ ከተሰጣቸው መሪ ዓላማ ውስጥ በቃጣናው አገራት የመሠረተ ልማትን ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በሙሉ አቅሟ እንደምትሳተፍ አረጋግጠዋል፡፡

ቤጂንግ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ኢንቨስትመንት ተኮር የጋራ እድገት እንዲሁም በአፍሪካ አገራት እያካሄደች ያለው የጋራ ልማት እንቅስቃሴ ለሩቅ ምስራቅ አገራት ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ እንደማጥበቂያ ብሎን ነው ብለዋል ፕሬዚደንቱ።

የኢስያ አገራት ጥምረት መጠናከር ደግሞ አገራቱ በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ እና  የበላይነትን እንዲጎናፀፉ ይረዳቸዋል ነው ያሉት፡፡

ተቋማቱ በጋራ መሥራታቸው እና ጥምረታቸውን ማጠናከራቸው በኢስያ አገራት መካከል ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲመሠረት የማድረግ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢስያ አገራት የመሠረተ ልማት ለማሟላት የመሥራት ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ በጥምረታቸው የሚተገበር ነው፡፡

አህጉር ተሻጋሪ ግንኙነት የመመስረት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅርበት መሥራት ይኖርባችኋል ሲሉም ፕሬዚደንቱ አሳስበዋል፡፡

ጥምረቱን ለማጠናከር አገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን እና የመንግስታቸው ድጋፍ እንደማይለይም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳካት በተያዘው እቅድ ውስጥ ቻይና የበኩሏን እየተወጣች እንደሆነ ነው ዢ የተናገሩት፡፡

አገሪቱ አሁን ላይ በዓለማቀፍ ደረጃ እያስመዘገበች ያለው እድገት ለዚህ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚደንቱ ቻይና ከምዕራቡ አገራት እና ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከርም የተቋማቱ አብሮ መስራት ሚና አለው ብለዋል፡፡

የኢስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ጥምረት እና የደቡብ ምስራቅ ኢስያ አገራት ህብረት የጋራ የምክክር መድረካቸውን እያካሔዱ ይገኛሉ፡፡( ምንጭ:የሲ ጂ ቲ ኤን )