ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት አባላት ወደ ሱዳን ሊያቀኑ ነው ተባለ

ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት አባላት በዚህ ሳምንት ወደ ሱዳን እንደሚያቀኑ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስታወቀ።

በአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ የሆኑት ቲቦር ናጊ፣ "ንፁሐን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን" ብለዋል።

የሽግግር መንግሥቱን የሚመራው ወታደራዊ ኃይል ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ በሚል ከእሁድ እለት ጀምሮ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ ሲሆን፣ በአድማው የመጀመሪያ ቀን አራት ሰዎች ከወታደሮቹ በተተኮሰ ጥይት መሞታቸው ታውቋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚስተር ናጊ "ሁለቱ ወገኖች መነጋገር የሚችሉበትን ከባቢ ለመፍጠር ይሰራሉ" ብሏል።

በተጨማሪም የሽግግር መንግሥቱንና ተቃዋሚዎችን ለማደራደር ጥረት ካደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር እንደሚነጋገሩ ታውቋል።

ሰኞ ዕለት የካርቱም ጎዳናዎች ፀጥ እረጭ ብለው ነበር የዋሉት። በርግጥ አንዳንድ ሱቆችና አውቶቡሶች አረፋፍደው ስራ የጀመሩ ቢሆንም ከሞላ ጎደል በከተማዋ በአድማው ምክንያት ሁሉ ነገር ተስተጓጉሎ እንደነበር ተገልጿል።

የሱዳን የሙያ ማህበራት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ባንኮች፣ ገበያዎችና ሱቆች በዋና ከተማዋ ካርቱምና በሌሎች ከተሞች የሥራ ማቆሙን ተቀላቅለው ነበር።

የሙያ ማህበሩ ከአንድ መቶ በላይ የተቃውሞ ሠልፈኞች ከተገደሉ በኋላ ነው ጥሪውን ያቀረበው።

"ሕዝባዊ አመፃችን የሲቪል አስተዳደር ስልጣን መረከቡን በቴሌቪዥን ቀርቦ እስኪናገር ድረስ ይቀጥላል" ብሏል ማህበሩ ባወጣው መግለጫ።

"ሰላማዊ አመፅ አምባገነን መሪዎችን እንዲንበረከኩ የሚያደርግ ብርቱ መሳሪያ ነው" ብሏል በመግለጫቸው።

ተቃዋሚ ሰልፈኞች አውራ ጎዳናዎችን የዘጉ ሲሆን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዳለ ሲገልፁ ነበር።

ሶስት የአማፂያን መሪዎችም ከሱዳን ወደ ደቡብ ሱዳን መወሰዳቸውም ተሰምቷል።

ከሶስቱ አንዱ የሆነው ያሲር አርማን ወደ ሱዳን የተመለሰው በሌለበት ሞት ከተፈረደበት ከአመታት በኋላ ባለፈው ሳምንት ነበር።

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)