ኡጋንዳ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባት ተገለጸ

ኡጋንዳ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ መስራት ይጠበቅባታል ተብሏል፡፡ 

ከ73 በመቶ በላይ ኡጋንዳዊያን ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅ የመታጠብ ባህል እንደሌላቸውም ተመልክቷል፡፡ 

27 ከመቶ ኡጋንዳዊያን ብቻ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ አጃቸውን በሳሙና ይታጠባሉ ነው ያሉት የሃገሪቱ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ጃኔ ሩት አሴንግ፡፡

በተለይም በወንዶቹ ላይ ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡

በዚህም ምክንያት እንደ ታይፎይድ፣ ኮሌራና ተቅማጥ ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ስንጋለጥ ቆይተናል፡፡

እጅግ በርካታ ዜጎቻችንንም በነዚህ በሽታዎች አጥተናል ብለዋል ዶክተር አሴንግ ለሃገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፡፡

በመሆኑም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በማንኛውም የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎቻችን መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጅ የመታጠብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

መንግስትም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና የጤና ቡድኖች ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡ 

ለኡጋንዳዊያን ወንዶች አክብሮት አለኝ፣ ይሁን እንጂ ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅ የመታጠብ ባህላቸውን በእጅጉ ማሳደግ ይኖርባቸዋልም ብለዋል በንግግራቸው፡፡

የሃገሪቱ ፓርላማም ለዚህ አሳሳቢ ችግር ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል ሚኒስትሯ፡፡

ሚኒስትሯ ከፓርላማ ንግግራቸው በኋላም ለዴይሊ ሞኒተር በሠጡት መግለጫ አብዛኞቹ ኡጋንዳዊያን ወንዶች እጅ የመታጠብ ልምድ የላቸውም፡፡

ለዚህ ደግሞ ወንዶቻችን የጉዳዩን አደገኝነት አለመረዳታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡( ምንጭ: ዘሞኒተር)