ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሃምቡርግ የቡድን ሃያ አገራት ስብሰባ ትልቅ ፈተና እንደሚገጥማቸው ተመለከተ

በሀምቡርጉ የቡድን ሃያ አገራት ስብሰባ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትልቅ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩስያው አቻቸው ጋር በአካል ይገናኛሉ፡፡ሁለቱ መሪዎች በአሜሪካ ምርጫና በዩክሬን ጉዳይ ዙርያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡  ጉባዔው በዋናነት በፓሪስ የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ዙርያ ይመክራል ነው የተባለው፡፡

ዛሬ በተጀመረው የቡድን ሃያ አገራት ስበሰባ ላይ ለመገኘት ፖላንድ ጎራ ብለው ያለፉት ፕሬዚዳንት ዶናድ ትራምፕ የምዕራባውያኑ ስልጣኔ አደጋ ታጋርጦበታል ብለው ነበር፡፡

በፖላንድ ዋርሶው ባደረጉት ንግግር ምዕራባውያኑን የወረፉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛሬ በሀምቡርግ ትልቅ  ፈተና ይገጥማቸዋል ሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

በተለይም የከባቢ አየር ንብት ለውጥ ላይ ያሳዩት ያልተጠበቀ አቋም በቡድን ሃያው አገራት መሪዎች ለፕሬዚዳንቱ ከሚቀርቡ ሞጋች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሚዛን የሚደፋ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

የበለፀጉት አገራት የከባቢ አየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የደረሱበትን መግባባት አልቀበልም ያሉት ትራምፕ በተለይም ከእንግሊዝና ከጀርመን ጠንካራ ትችት ይጠብቃቸዋል፡፡

የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ማርኬል የቡድን ሃያው ስብሰባ ዋና አጀንዳ የፓሪሱን የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ብለዋል፡፡

እናም አሜሪካ ከፓሪሱ የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንድትወጣ ላደረጉት ፕሬዚዳንት ትራም ጉባዔው ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ሌላው ጉዳይ ደግሞ ትናንት በዋርሶ ከወረፏቸው ከሞስኮው አቻቸው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ይገናኛሉ፡፡

ይህም በጉጉት የሚጠበቅ ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ የሁለቱ መሪዎች ግንኙነትን ተጠባቂ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ፕሬዚዳንት ትራምፕን ወደ ሥልጣን ያመጣው የ2016 የአሜሪካ ምርጫ ተጠቃሽ ነው፡፡

ሩስያ የዲሞክራቲክ ፓርቲዋ የትራምፕ ዋና ተፎካካሪ የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን በምርጫው እንዲሸነፉ የስውር እጇን በማስገባት በምርጫው ያልተጠበቀ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጋለች በሚል በተደጋጋሚ ትከሰሳለች፡፡ ሩስያ ክሱን ከእውነታ የራቀ ነው በማለት ብታጣጥለውም፡፡

እናም ሁለቱ መሪዎች ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ሲያወዛግብና ሲያነጋገር በቆየውና፤ እስከ አሁን ድረስም ግልፅ ምላሽ ባልተገኘበት  ጉዳይ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም  በተጨማሪ ትራምፕ በዋርሶ ንግግራቸው ሩስያ ዩክሬንን ከማተራመስ ልትታቀብ ይገባል በሚል የሰነዘሩት ሐሳብ በሩስያው አቻቸው ለውይይት ሊቀርብ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በአካል ተገናኝተው መምከራቸውና መወያየታቸው ቀደም ሲል በየፊናቸው በሚሰነዝሩት ትችት ዙርያ ተቀራርቦ ለመነጋገርና ቀጣይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር  ይረዳል ነው የተባለው፡፡

በሀምቡርጉ ጉባዔ የተለያዩ መሪዎች ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  የዋሸንግተን፣ የለንደን፣ የበርሊንና የሞስኮ፣ መሪዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች ይጠበቃሉ።

ጉባዔው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ጀርመን የፀጥታ ኃይሏን ያጠናከረች ቢሆንም ከስምት ሺ በላይ ሰዎች ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ መውጣታቸውም ነው የተሰማው፡፡ በዚህም በሰልፈኞቹና በፖሊስ መካከል በተከሰተው ግጭትም 111 የፖሊስ አባላት መጎዳታቸው ተሰምቷል፡፡