አሜሪካ ኤርትራን ጨምሮ በአራት አገራት ላይ የቪዛ እገዳ ለመጣል መዘጋጀቷን አስታወቀች

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም አስተዳደር በአራት አገራት ላይ የቪዛ እገዳ ለመጣል በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገለፀ።

የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤትን ዋቢ ያደረገው የሲ ኤን ኤን ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የቪዛ ገደብ የሚጣልባቸው አገራት ኤርትራ፣ ጊኒ፣ ሴራሊዮን እና ካምቦዲያ ናቸው።

ምን ዓይነት የቪዛ ማእቀብ እነዚህ አገራት ይጣልባቸዋል የሚለውን ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በቀጣይ ይወስናል ነው የተባለው።

የሚጣለው የቪዛ ገደብ ምናልባት የአገራቱን የትኛውንም ዜጋ የሚመለከት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

በተጨማሪም ቻይና፣ ኩባ፣ ቬትናም፣ ላኦስ፣ ኢራን፣ በርማ እና ሞሮኮ በዩናይትድ ስቴትስ ወንጀል በመፈፀማቸው የሚባረሩ ዜጎቻቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ አገራት ናቸው ተብለው ተዘርዝረዋል።

በአጠቃላይ 23 አገራት አሜሪካ የምታባራቸውን ዜጎቻቸውን ላለመቀበል የወሰኑ አገራት አሉ።

ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት እነዚህን አገራት አሜሪካ እንድትቀጣ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።