የአፍሪካ ኢንተርኔት ገበያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ እንደሚያድግ ተመለከተ

በአፍሪካ የሞባይል ኢንተርኔት ገበያ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ በእጥፍ እንደሚያድ አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡    

በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር እና ፈጣን የኢንተርኔት መኖር ለዕድገቱ ትልቁን ሚና ይጫወታልም ነው የተባለው፡፡

በለንደን የሚገኘው ኦቨን ኩባንያ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው በአፍሪካ  የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ተመዝግቦበታል፡፡ ጥናቱ  እንዳለው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ419 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሆኗል፡፡

እንደ ኩባንያው ገለጻ ከሆነ ይህ ቁጥር እኤአ በ2020 በእጥፍ በመጨመር አንድ ቢሊዩን የሚደርሱ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ይኖራሉ ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ በአፍሪካ ያለውን የኢንተርኔት ገበያ በእጥፍ ያሳድገዋል ሲል የቡልበርግ ዘገባ ያጠናክራል፡፡

በአፍሪካ የዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች መበራከትና ፈጣን የኢንተርኔት አቅርቦት መስፋፋት ለኢንተርኔት ገበያ መበራከት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ወደፊት ከአገልግሎቱ ጋር የተያያዘ መልካም የሚባል የገበያ ትስስር ይፈጠራል ብሏል ዘገባው፡፡ 

ይሁን እንጂ የአፍሪካን የኢንተርኔት ገበያን ሊያቀዛቀዙ ይችላሉ ተብለው የሚፈሩ ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥናቱ  ሳይገልፅ አላለፈም፡፡

ከስጋቶች መካከል በአፍሪካ የሚሸጡ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በአብዛኛው ኦርጅናል ያለመሆናቸዉ እና በየቦታዉ ኦርጂናል ያልሆኑ ስልኮች መመረት አንዱ ማሳያ ሆኖ ተወስዷል፡፡

ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት እንኳን በአንድ አመት ዉስጥ ከተሸጡ ስልኩች መካከል ስልሳ በመቶ የሚሆነው ኦርጅናል ያልሆኑና የተበላሹ  ስልኮች መሆናቸው  ተመልክቷል፡፡

በኬንያ በ2012 የፈረንጆቹ ዓመት1ነጥብ5 ሚሊዩን የሚደርሱ ኦርጅናል ያልሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡  

የአፍሪካ ትልቁ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ሽያጭ በሚከናወኑበት በናይጄሪያ እንኳን ከ15 ሚሊዩን ተጠቃሚዎች ዉስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ኦርጅናል ያልሆኑ ስልኩችን ይጠቀማሉ፡፡ይህ ደግሞ በአፍሪካ ያለውን የኢንተርኔት ገበያ ከታሰበው በላይ እንዳይራመድ ተጽዕኖ ይፈጥራል ተብሏል፡፡

እነዚህ ችግሮች መበራከታቸው የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን የዓለምን የኢንተርኔት ገበያ በእጅጉ ይጎዳል ተብሏል፡፡

በአህጉሪቱ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡን  ያመላከተው የኩባንያው ጥናት አሁን ላይ እንደ ኤም ቲ ኤን እና ኦሬንጅ ያሉ ኩባንያዎች ከተጠቃሚዎች ቁጥር መብዛትና ከአገልገሎቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአህጉሪቱ የተሻለ የተንቀሳቃሽ ስልኮች   ኢንተርኔትን ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑ ይነገራል።ይህም በአህጉሪቱ ያለዉን የኢንተርኔት ገበያ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡