ስኮትላንድ ለአሜሪካ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

ስኮትላንድ ለአሜሪካ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ልትገነባ  መሆኑ ተገለጸ ።

ስኮትላንድ የምትገነባው የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 4 መቶ ሺህ የአሜሪካ ቤቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

ሀገራት ከውሃ ኃይል፣ከነፋስ ፣የፀሃይ ብርሃን፣ ከባዮጋዝና ከመሳሰሉት የኤሌክትሪክ ፍጆታን ያገኛሉ ፡፡          

አሁን በርካታ ሃገራት በስፋት ለመጠቀም ፍላጎታቸውን እያሳዩበት ያለው የነፋስ ኃይልም የኤሌክትሪክ ፍጆታን በመጨመር የሚያስገኘው ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ከፍ ያለ ነው፡፡

በዓለማችን ትልቁ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በእንግሊዝ እየተገነባ ሲሆን 230 ሺህ ቤቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡  የሚገነባው የኃይል ማመንጫ 32 ተርባይነሮች ያሉት ሲሆን ሁሉም ተርባይነሮች አንድ ጊዜ ብቻ በሚያደርጉት መሽከርከር ለ29 ሰዓታት የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ፡፡   

በታላቋ ብሪታኒያ ግዛትና ስኮትላንድ በስፋት የሚጠቀሙበት የነፋስ ኃይል ማመንጫ ወደ አሜሪካም እየተስፋፋ ነው፡፡ ስኮትላንድ ለአሜሪካ ለመገንባት ስምምነት ላይ የደረሰችበት የነፋስ ኃይል ማመንጫ 400 ሺህ ቤቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡  

ይህው የነፋስ ኃይል ማመንጫ 2 ጣቢያዎች አሉት፡፡ ሁለቱ ጣቢያዎች በማሳቹሴትስ እና በሰሜን ካሊፎርኒያ አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ በእንግሊዝ ከሚገኘው ጣቢያ ከፍ ያለ የኃይል መጠን  ያመነጫል ተብሎለታል፡፡ የማሳቹሴትስ የኃይል ማመንጫ እኤአ በ2022 እና የሰሜን ካሊፎርኒያው እኤአ በ2025 ኃይል አገልግሎት መሥጠት ይጀምራሉ፡፡

ኩባንያው ለሁለቱም ጣቢያዎች በምን ያህል ክፍያ ለመሥራት እንደተስማማ ይፋ አላደረገም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ለነፋስ ኃይል ልማቱ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

ኬዝ አንደርሰን የስኮትላንድ ነፋስ ኃይል ኮርፖሬት ሥራ አስኪያጅ የነፋስ  ኃይል ኢንደስትሪው ወደ ውጭ የመላክ አቅሙን ያዳበረ ውጤታማነቱን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

በአገረ  እንግሊዝ የሚገኘው የነፋስ ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂውን በማዘመን የውጭ ገበያውን በመሪነት በመያዝ አሁንም ገቢውን ለማሳደግ እንደሚሰራ ኩባንያው አሳውቋል፡፡ 

በአሜሪካ ለኃይል ማመንጫ የሚውሉ ሰፋፊ መሬቶች በተለያዩ የግዛት ዳርቻዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች ቢኖሯትም  አሜሪካ እስካሁን ፈቃደኛ አልነበረችም ፡፡ አሁን ላይ ነፋስ ኃይሉን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ሰርተን እናሳያቸዋለን ብለዋል፡፡ 

የሁለቱ ሃገራት የንግድ ግንኙነትም እያደገ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ( ምንጭ: ቢቢሲ)