ኳታር የተጣለባትን ማዕቀቦች የመቋቋም ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዳላት ገለጸች

ኳታር ከጎረቤቶቿ የተጣለባትን ማዕቀቦች ለመቋቋም የሚያስችል ኤኮኖሚያዊ አቅም እንዳላት የሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

ፈርጣማ የምጣኔ ሃብት ባለቤት የሆነችው ሳኡዲ አረቢያን ጨምሮ ሌሎችም የባህረ-ስላጤ ሃገራት አሸባሪዎችን ትረዳለች በሚል የተለያዩ ማዕቀቦችን በኳታር ላይ መጣላቸው ይታወሳል፡፡

ማዕቀቡን ተከትሎም ኳታር ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት እንደምትፈልግ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷም አይዘነጋም፡፡

በዚህም መሰረት ኳታር ማዕቀቡ እንዲነሳላት ከፈለገች ግዙፉን የሚዲያ ተቋሟን አልጀዚራን ከመዝጋት አንስቶ ሌሎችንም በርካታ ቅድመ-ሁኔታዎች እንደታሟላ ሃገራቱ ቢጠይቋትም ይህ ለኳታር ሉዓላዊነት እውቅና መንፈግ ነው በሚል ኳታር ቅድመ- ሁኔታውን ውድቅ ማድረጓም ይታወሳል፡፡ 

የኳታር ዉሳኔ ያልተዋጠላቸው ሳኡዲ አረቢያና አጋሮቿ በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው በኳታር ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ይበልጥ በማጥበቅ ሀገሪቱን ለችግር መሪዎቿን ደግሞ ለውጥረት ለመዳረግ ዶልተውም ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም ዓለም የኳታር መጨረሻ ምን ይሆን እያለ በሚጠብቅብት በዚህ ወቅት ነው የኳታር ማዕከላዊ ባንክ ኳታር ጎረቤቶቿ የጣሉባትን ማዕቀብ ለመቋቋም የሚያስችል ግዙፍ ኢኮኖሚ እንዳላት ነው ያስታወቀው፡፡   

ኳታር ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ እና ከጎረቤቶቿ የሚደርስባትን ማንኛውም ጫና ለመቋቋም የሚውል 340 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መመደቧን ነው ባንኩ ያስታወቀው፡፡

የማዕከላዊ ባንኩ ዋና አስተዳዳሪ ሸይክ አብዱላሂ ቢን ሳዑድ አል-ታኒ እንደገለጹት ኳታር እንደማንኛውም ሃገር በሉዓላዊነቷ አትደራደርም፡፡

“ይህ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፤ ኳታር ማንኛውንም አይነት ውጫዊ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅም አላት፡፡” ብለዋል ከሲ ኤን ቢ ሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

እንደ አል-ታኒ ገለጻ ኳታር የተጋረጠባትን ፈተና ለመቋቋም ማዕከላዊ ባንኩ 40 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላርና ተጨማሪ ወርቅ እንዲሁም የኳታር ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ደግሞ 300 ቢሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡

ከማዕቀቡ በኋላ የኳታር ንግድ የተቀዛቀዘ ሲሆን የሪያሏም ዋጋ ተለዋዋጭ ሆኗል፡፡

አሁንም ቢሆን የኳታር የገቢ ምንጮች እንዳልደረቁ ግን አል-ታኒ ይናገራሉ፡፡

“ኳታር ዛሬም በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ ማግኘቷን ቀጥላለች፤ የነዳጅና ዘይት ንግድ ተቋሞቻችን የረጅም እና የአጭር ጊዜ የንግድ ውሎችን በመዋዋል ያለምንም ችግር ገቢ እያስገኙልን ነው ”

ኳታር ዋነኛዋ የነዳጅ ላኪ ሃገር መሆኗን እና በተለይም ከማዕቀቡ በኋላ የነዳጅ ምርቷን እና ገበያዋን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የገበያና የኢኮኖሚ ተንታኞች መስክረዋል፡፡( ምንጭ: ሮይተርስ)