ሰሜን ኮርያ የተባባሩት መንግሥታት ማዕቀብ ሉዓላዊነትን የሚጻረር መሆኑን ገለጸች

ሰሜን ኮርያ የተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ ሉዓላዊነቴን የሚፃረር ነው አለች፡፡

ደቡብ ኮርያ ያቀረበችው የእንወያይ ጥያቄም ከአንገት በላይ ነው በማለት ሰሜን ኮርያ  አጣጥለዋለች ፡፡ ቤጂንግ ፒዮንግያንግ ጥያቄውን መግፋት እንደሌለባት አሳስባለች፡፡

የተባበሩት መንግስታትን ማዕቀቦች እንዳሻት በመተላለፍ የኒውክሌር ልማትን የምትጧጡፈውና ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎችን በምታደርገው ሰሜን ኮርያ ላይ የመንግስታቱ ድርጅት አዲስ ማዕቀብ ጣለ፡፡

አዲሱ ማዕቀብ አገራት ከፒዮንግያንግ የድንጋይ ከሰልን፣የባህር ምግብ፣ ብረትና ሌሎች ማዕድናትን እንዳያስገቡ ይከለክላል፡፡ በዚህም ሰሜን ኮርያ በየዓመቱ ከወጭ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ታጣለች፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሰሜን ኮርያም ሠራተኞችን እንዳይቀበሉ፤ ከሰሜን ኮርያ ጋር አዲስ ግንኙነት በመፍጠር ማልማትና በጋራ መስራትም ለአገራት አይፈቀድም፡፡

ሰሜን ኮርያ በበኩሏ የመንግስታቱ ድርጅት ማዕቀብ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ማዕቀቡን አጣጥላዋለች፡፡ የፒዮንግያግን ሉዓላዊነት የሚፃረር እርምጃ ነው ስትልም ወቀሳ አቅርባለች፡፡

የደቡብ ኮርያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ዩንግ በፊሊፒንስ በተካሄደው የቀጣናው አገራት ስብሰባ ላይ ለሰሜን ኮርያው አቻቸው ሪ ዮንግ ሁ የእንወያይ ጥያቄውን አቅርበውላቸዋል፡፡

የፒዮንግያንጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ጥያቄውን ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡

ቻይና በበኩሏ ሰሜን ኮርያ የጎረቤቷ ደቡብ ኮርያን ጥያቄ በአዎንታዊነት ልትቀበለው እንደሚገባ አሳባለች፡፡ የደቡብ ኮርያ ተነሳሽነትን ያደነቀችው ቤጂንግ ለውይይቱ ስኬት የሚጠበቅባትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ገልፃለች፡፡

ሰሜን ኮርያ በተጠናቀቀው ሐምሌ ወር ብቻ ሁለት አህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤሎች ሙከራ አድርጋለች፡፡ የሚሳኤሎቹ ሙከራ ከአሜሪካ ለሚሰነዘርባት ዛቻና ማስፈራሪያ ምላሽ መስጠትን ያለመ እንደሆነም መገለፁ ይታወሳል፡፡

ፒዮንግያግ በቅርቡ የሞከረችው አህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤል ኒው ዮርክና አላስካን የመሳሰሉ የአሜሪካ ዋና ከተሞችን መምታት የሚችሉ መሆኑንም ቢቢሲ በዘገባው ለትውስታ አቅርቧል፡፡ 

ሰሞኑን የፀጥታው ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው ማዕቀብ በቻይናና ሩስያም ሙሉ ድጋፍ ማግኘቱ በተለይም አሜሪካን በከፍተኛ ደረጃ አስደስቷል፡፡