ሩሲያና አሜሪካ ወታደራዊ ኃይላቸውን ከሶሪያ ምድር እንዲያስወጡ ፕሬዚዳንት ጣሂር ኤርዶጋን ጥሪ አቀረቡ

ሩሲያና አሜሪካ ወታደራዊ ሀይላቸውን ከሶሪያ ምድር እንዲያስወጡና የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ከጦር ቀጠና ውጭ በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲቭ ጣሂር ኤርዶሀን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ይህንን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ለሶሪያ ዘላቂ ሰላም መፍትሄው ወታደራዊ ዘመቻ ሳይሆን ውይይትና መደራደር ነው ብለው ከተስማሙ በኋላ ነው፡፡

ሶሪያ ከአሸባሪው አይ ኤስ ትርምስ እየወጣች ስትመጣ በበሽር አላሳድ መንግስትና በአማፂያኑ ቡድኑ መካከል ያለው ግብ ግብ ግን አሁንም ሀገሪቷ በሁለት እግሯ እንዳትቆም አድርጓታል፡፡

በሶሪያ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት እጃቸውን በረጅሙ የዘረጉት አሜሪካና ሩሲያ ግን ሀገሪቷን ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ ወታደራዊ ዘመቻቸውን አቁመው በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዳለባቸው ያምናሉ ።

በሶሪያ ለተከታታይ አመታት ያክል ሊረግብ ያልቻለውን ጦርነት ገቶ በሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ትኩረት ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲቭ ጣሂር ኤርዶሀን በተያዘው አመት ብቻ እንኳን ወደ ሩሲያ አራት ጊዜ ተመላልሰው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡

የኤርዶሀን ይህን ሁሉ ጊዜ ወደ ሩሲያ ማቅናት ግን በሶሪያ የኩርዲስቶች የእንገንጠል ትግላቸው በቱርክ ያሉ ኩርዶችንም ልብ ሊያሸፍት ይችላል በሚል ስጋት እንጂ ለሶሪያ ሰላም በማሰብ አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም እየተሠጡ ነው፡፡

በሶሪያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ወታደራዊ ዘመቻ አማራጭ መፍትሄ መሆን አልቻለም በማለት አሜሪካና ሩሲያ ወታደሮቻቸውን ከሶሪያ ምድር እንዲያስወጡ ለመምከር ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ወደ ሩሲያዊዋ ሶቺ ከተማ በማቅናት ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መክረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በአሁኑ የሩሲያ ጉዟቸው አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገሪቱን በወታደራዊ ቀጠና ማጥለቅለቅ መፍትሄ አይደለም ይልቁንስ ለስምምነትና ድርድር እንቀመጥ ብለው ከተወያዩ  በኋላ  ያለውን ቀጣይ ውሳኔ ለማስፈፀም ነውም ተብሏል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ከሆነ ትራምፕና ፑቲን በሶሪያ ይህንን ተመሳሳይ አቋም ካንፀባረቁ ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ሁለቱ ሀገራት ወታደሮቻቸውን ከሶሪያ በአፋጣኝ እንዲያስወጡ ለማድረግና ለሶሪያ መረጋጋት የሚበጀውን ሌላ መፍትሄ እንዲያበጁ ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት፡፡

አሜሪካና ሩሲያ ከሰሞኑ በቬትናም ክሪሚሊን በተካሄደው የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ቀጠና ውይይት ላይ ለሶሪያ በሚበጀው ቀጣይ መፍትሄ ላይ መስማማታቸው ሶሪያን ወደ ሰላም ሊያመጣት ይችል ይሆናል የሚሉም አልጠፉም፡፤ ይህ የሚሆነው ግን በቃላቸው መሰረት ወታደሮቻቸውን አስወጥተው በውይይት ከሆነ ነውም ተብሏል ፡፡

በሁለቱ ሀያላን ስምምነት እና በኤርዶሀን ጥሪ መሰረት በሽር አላሳድ መንግስትን የምትደግፈው ሩሲያ ያሰማራቸውን ጦር ከሶሪያ ቀድማ እንደምታስወጣ ይጠበቃል፡፡ አሜሪካ በበኩሏ በሶሪያ ለኩርዶች ድጋፍ ያስገባችውን ጦርም ከሶሪያ ምድር ጠራርጌ አስወጣለሁ ብላለች ፡፡

ከቱርክ፣ሩሲያ ባለፍ ኢራንም በሶሪያ መረጋጋትን ለማስፈን የበሽር አላሳድ መንግስትን ትደግፍበት የነበረውን ጦሯን ለማሥወጣት በአንካራ መክረዋል፡፡ ቱርክ በበኩሏ የአላሳድን መንግስት ለመጣል በሶሪያ የሚገኙትን የአማፂ ቡድን ትደግፍ የነበረ ሲሆን ወታደራዊ ሀይሏን እንደምታስወጣ ነው የተገለፀው፡፤

በሶቺ በሚካሄደው የኤርዶሀንና ፑቲን ውይይትም ከሶሪያ ሰላምና መረጋጋት ባለፈ በሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ላይም እንደሚያተኩር ተጠቁሟል፡፡

የኤርዶሀን በዚህ አመት ወደ ሩሲያ 4 ጊዜ መመላለሳቸው ከሁለት አመት በፊት ቱርክ የሩሲያን አውሮፕላን በደቡባዊ ቱርክ አካባቢ መታ በመጣሏ ሩሲያ በቱርክ ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ለመቀነስና ከዚህ ቀደም ሻክሮ የነበረውን ግንኙነታቸውን ለማደስ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል፡፡ ( ምንጭ: አልጀዚራ)