ጀርመን የጥምር መንግሥት ለማቋቋም እያደረገች ያለችው ድርድር ከሸፈ

ጀርመን የጥምር መንግሥት ለማቋቋም እያደረገች ያለው ድርድር መክሸፉ ተገለጸ ።

ጀርመን የጥምር መንግስት ለማቋቋም እያደረገቸው በነበረው የድርድር  ሂደት  ውስጥ የፍሪ ዴሞክራቲክ  ፓርቲ  እራሱን ማግልሉን ተከትሎ  መራሂተ መንግስት አንጌላ  ሜርክል ችግር ውስጥ መውደቃቸው  ተገለጸ፡፡

የነጻ ገበያ ፖሊሲን የሚከተለው ፕሮ ቢዝነስ ፍሪ ዴሞክራቲክ ፓርቴ (FDP) ሊበራል ፓርቲ ከድርድሩ ራሱን ያገለለው ከመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወግ አጥባቂ  ፓርቲ ጋር መተማመን በማጣቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ጀርመንን በቀጣይ የሚያስተዳድረውን የጥምር መንግስት ለመመስረት እየተካሄደ በነበረው የድርድር መድረክ  የአንጌላ ሜርክል  ወግ አጥባቂ  ፓርቲ ፤ ፕሮ ቢዝነስ ፍሪ ዴሞክራቲክ እና አረንጓዴ ፓርቲ በስደተኞች ጉዳይ እና በኃይል ፖሊሲ ዙሪያ ከስምምነት ባለመድረሳቸው ድርድሩ ሊቋረጥ ተገዷል፡፡


 
ተደራዳሪ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ዘመናዊነትን እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ የአስተዳደር ስርዓትን ለመመሥረት የጋራ ራዕይ የላቸውም ሲሉ የፓርቲው መሪ የሆኑት ክርስቲያን ሊንደር ተናግረዋል፡፡ በዚህም ፓርቲያቸው ከድርድሩ እራሱን እንዳገለለ አስታውቀው አግባብ ያልሆነ  የአስተዳደር ስርዓትን ከመዘርጋት ይልቅ አለማስተዳደር ይመረጣል ብለዋል፡፡

 
ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በመጪው መስከረም የሚካሄደውን የሀገሪቱን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ የክርስቲን ዴሞክራቲክ ዩኒየን ፤ ክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን ፤ ዘ ፕሮ ቢዝነስ ኤፍዲፒ እና የአረንጓዴ ፓርቲን በማካተት የጥምር መንግስት ለመመስረት እየሰሩ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል ፡፡

 
የድርድሩ መፍረስ እንደ ታሪካዊ ቀን ሊወሰድ ይችላል ያሉት ቻንስለሯ ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ በስደተኞች እና በኃይል ፖሊሲ ዙሪያ የተለያየ አቋም ቢይዙም ከስምምነት ላይ መድረስ ይገባቸው ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲውም ከድርድሩ እራሱን በማግለሉ ሊጸጸት ይገባል ብለዋል፡፡ 

ቻንስለሯ አያይዘውም የድርድሩን መፍረስ ተመልክቶ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውን ጠቁመው እንደ መሪነቴ የጀርመንን የወደፊት እጣ ፈንታን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ ማንኛውንም አይነት እርምጃና ውሳኔ ከማሳለፍ አልቆጠብም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይህ የጥምር መንግስት ለጀርመን መንግስት አዲስ የአሰራር ስርአትን ይዘረጋል ተብሎ የታመነበት ሲሆን  ቀደም ሲልም በክልል ደረጃ ሙከራ ተደርጎበታል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ ከፍተኛ ፖለቲካዊ አጀንዳ መሆኑ የቀጠለ ሲሆን ወራቶችን በፈጀው በዚህ ድርድር ላይም እ.ኤ.አ በ2015 እና በ2016 ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ተሰደው መዳረሻቸውን ጀርመን ያደረጉ 1ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች  ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተመልሰው መገናኘት አለባቸው በሚል ክርክር የተካሄደ ሲሆን  ጀርመን ለስደተኞች ድንበሯን ክፍት ማድረግ አለባት የሚለው የአንጌላ ሜርክል ውሳኔም ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

የአረንጓዴ ፓርቲ ጀርመን ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ድንበሯን ክፍት ያደረገችላቸው ስደተኞችን ቁጥር እስከ 200ሺ ድረስ  ብቻ መገደብ አለባት የሚል አቋሙን አስቀምጧል፡፡

ፓርቲዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ አቋም ላይ ለመድርስ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ሲሆን የአረንጓዴ ፓርቲ የከሰል ድንጋይን በመጠቀም ኃይል የማመንጨት ስራ ከ 8-10 ሜጋ ዋት ድረስ መውረድ እንዳለበት ሲሟገት ቀሪዎቹ ፓርቲዎች ደግሞ ይህ ውሳኔ የኃይል ኢንዱሰትሪው ላይ እና በአምራች ዘርፉ ላይ የስራ አጥነትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ውድቅ አድርገውታል፡፡

የድርድሩን መፍረስ ተከትሎ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ከአረንጓዴ ፓርቲ ወይም ከ ከኤፍ ዲፒ ፓርቲ ጋር ሌላ መንግስት ለማቋቋም እና ከሌሎች ፓርቲዎች እንዲሁም ከግለሰቦች ድጋፍን ለማሰባሰብ ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ዘገባው አመላክቷል፡፡ 

ይህን ድርድር ከግብ ለማድረስ ብዙ አማራጮች ቢሞከሩም አልተቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር እስቴንሜር አሁን በስራ ላይ ያለውን ፓርላማ በማፍረስ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ማዘዝ ይኖርባቸዋል ሲሉ የሶሻል ዴሞክራት መሪ የሆኑት ማርቲን ሽሉዝ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሳምንታት የተካሄደው የፓርቲዎቹ ክርክር በፖሊሲ ልዩነቶች ላይ ያተኩር እንጂ ወደ ሥልጣን ሽኩቻ ሊያመራ እንደሚችል  የዘገበው ዘ ጋርዲያን ነው፡፡