የእስላማዊ ወታደራዊ ኃይል ጥምረት ሽብርተኝነትን ከመሠረቱ ለማጥፋት ይታገላል-ልዑል ቢን ሰልማን

የሳዑዲ አረቢያው ገዢ እና የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስተር ልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን የእስላማዊ ወታደራዊ ኃይል ጥምረት ሽብርተኝነትን ከመሠረቱ ለማጥፋት እንደሚታገል  አስታወቁ ፡፡

የእስላማዊ ወታደራዊ  ጥምረት አባል ሀገራት መከላከያ ሚኒስተሮችና ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች በሪያድ ተገናኝተው በመከሩበት ወቅትልዑል ቢን እንደተናገሩት ሽብርተኝነትን ከመሠረቱ  ለማጥፋት ጥምረቱ  ከፍተኛ ትግል  ያደርጋል ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ትልቅ ስጋት ከሆኑት መካከል ሽብርተኝነት በግንባር ቀደምትነት  የሚጠቀስ ሲሆን የተለያዩ አክራሪ ኃይሎች ስልቶቻቸውን በመቀያየርና የሽብር ጥቃቶችን በመሰንዘር ለብዙሃን ዜጎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በሽብር ጥቃት ከሚታመሱ የአለም አገራት መካከል ሊቢያ ፤ግብጽ ፤የመን ፤ሳዑዲ አረቢያና ኢራን ይጠቀሳሉ ። እነዚህ የአረብ ሀገራትም ይህን የሽብር እንቅስቃሴ ከመሠረቱ ለማጥፋት የወታደራዊ ኃይል ጥምረት አቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ 

ይህ የወታደራዊ ኃይል ጥምረትም ከተመሠረተ ሁለት አመታት አስቆጥሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 የተቋቋመው ይህ ኃይል በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ሲሆን፥ 40 አባል ሀገራትን አካቶ ይዟል፡፡  

የእስላማዊ ወታደራዊ ኃይል ጥምረቱ አረብ ሀገራት ለአለማችን ስጋት እየሆነ የመጣውን የሸብር ቡድን አይ ኤስ ለመዋጋት በቂ ጥረት እያደረጉ አይደለም እየተባለ የሚሰነዘረውን ትችት ለማስቀረት እና በተለያዩ ጊዜያት የሚሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶችን ለመግታት  መቀመጫውንም በሳዑዲ አረቢያዋ ሪያድ በማድረግ  እየሠራ ይገኛል ፡፡

ባለፈው አርብ በግብጽ ሰሜናዊ ሲናይ ግዛት ሱፊ መስጂድ ላይ በተሰነዘረ የሽብር ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን 128 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከሟቾቹ መካከልም 27 ህጻናት ናቸው፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ተሸክመው ወደ መስጂዱ በመዝለቅ ከፍተኛ ጥቃትን ሰንዝረዋል፡፡ ከመካከላቸውም የአሸባሪው አይ ኤስ ሰንደቅ ዓለማ ይዘው የታዩ ጥቃት ፈጻሚዎች በመኖራቸው ቡድኑ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት እየተነገረ ይገኛል፡፡

ይህን ጥቃት ተከትሎም የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሰልማን ለሳዑዲው አል አረቢያ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሠጡት አስተያየት ሽብርተኝነት ከመሠረቱ እስኪወገድ ድረስ የእስላማዊ ወታደራዊ ኃይል ጥምረት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ሲሊ ተናግረዋል፡፡

ሽብርተኞች ሰላማዊ ሀይማኖታችንን እንዲረብሹ አንፈቅድላቸውም ፤ ዛሬ ሽብርተኝነትን ከመሰረቱ ለመዋጋትና ለማጥፋት በትብብር እየሰራን መሆናችንን በጠንካራ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የተሰባሰብነው ሲሉ የጥምረቱ አባል ሀገራት መከላከያ ሚኒስተሮችና ከፍተኛ የደህንነት ሀላፊዎች በሪያድ ተገናኝተው በመከሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

እንደ አል አረቢያ ዘገባ ከሆነም ሽብርተኝነትን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ስራችንን በተጠናከረ መልኩ እንደምናከናውን ለማረጋገጥ እንወዳለን ሲሉ የሳዑዲው ልዑል አስረግጠው ተናግረዋል፡፡  ( ምንጭ:ሲኤን ኤን)