ኢራን የሚሳኤል ፕሮግራሟን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀያላን መንግስታት የማስፈራሪያ ዛቻቸውን የማያቆሙ ከሆነ ኢራን የተምዘግዛጊ ሚሳኤል ፕሮግራሟን አጠናክራ እደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

ኢራን ይህንን ያለችው ደግሞ ሀያላን ሀገራቱ አራን የ2015ቱን የኒዩክለር ስምምነት አፍርሰሻል በሚል እየወነጀሏት በሚገኙበት ጊዜ ነው፡፡

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀያላን መንግስታት ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ያላትን የበላይነት ለመቀልበስ ሲሉ ሁነኛ ምክንያት ያሉትን የሚሳኤል ፕሮግራሟን እንድትቀንስ ለማድርግ የተለያዩ ዘዴዎችን መዘየድ እንደፈለጉ አስቀድማ የተረዳችው ኢራን ከሚሳኤል ማምረት ፕሮግራሜ ማንም አያስቆመኝም እያለች ትገኛለች፡፡

ኢራን ይህንን ያለችው ደግሞ ሀያላን ሀገራቱ እኤአ የ2015ቱን የኒዩክለር ስምምነት አፍርሰሻል በሚል እየወነጀሏት በሚገኙበት ጊዜ ነው፡፡ በኒዩክለር ሀይል ከበለፀጉ ሀያላን ሀገራቱ መካከል ፈረንሳይ በኢራን የኒዩክለር መረሃ ግብር ስምምነት ላይ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል በማለት ከአሜሪካ ጎን መቆሟ ተሰምቷል ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ  ከሳውዲ አረቢያ ጋር ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ የሀይል የበላይነትን ለመያዝ እያደረገች ያለው ፉክክር የቀጠናው ሀገራትን ለቀውስ ዳርጓል ብላ ማመኗ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው የኃይል ሚዛን ለማመጣጠን ቴህራን ሚሳኤል የማምረት ሂደቷን ማሻሻያ ልታደርግበት ይገባል ሲሉ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ሀያላን ሀገራት ግን ከሰሞኑ ዝምታን መረጠዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ነው ኢራን ለአውሮፓ ሀያላን እና አሜሪካ  ዛቻና ማስፈረሪያ የሚሰነዝሩ ከሆነ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎችን ማምረት እቀጥላለሁ የሚል መልዕክትን ያስተላለፈችው፡፡

የኢራን መከላከያ ሀይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሁሴን ሳላሚ ለሮይተርስ እንደገለፁት አሜሪካና የአውሮፓ ሀያላን እኛን አቅም ለማሳጣት እየሞከሩ ነው፡፡ የተምዘግዛጊ ሚሳኤል ማምረት አቅማችንን ከ2ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እንዲወነጨፍ አድርገን የመስራት አቅም አለን፡፡ የቴክኖሎጅ ውስንነት  ኖሮብንም አይደለም  ዝምታን የመረጥነው፡፡ የተጠና ስልት እና ፍልስፍና ስለምንከተል ነው እንጂ ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሃሰን ሮሀኒ የአውሮፓ ሀያላን የቴህራንን የሚሳኤል ማምረት አላማ ካልተረዱ እና የአሜሪካን እና እስራኤልን አቋም ብቻ የሚከተሉ ከሆነ ቴህራን አሁንም ከዚህ በበለጠ መልኩ ሚሳኤል ለማምረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሮሀኒ አክለውም እስካሁን ድረስ የአውሮፓ ሀያላን ከፈረንሳይ ውጭ በሚሳኤል ፕሮግራማችን ላይ የማስፈራሪያ ዛቻ እንዳላደረሱብን ነው የሚሰማን፡፡ እኛ ከ2ሺህ ኪሎሜትር  በላይ የሚመምዘግዘግ የሚያስችል ሚሳኤል የመስራት ፍላጎት የለንም፡፡ የሚያስፈራሩን ከሆነ ግን መጨመር የሚያስችል በቂ እውቀት አለን ብለዋል፡፡

ኢራን በተደጋጋሚ የሚሳኤል ፕሮግራሜ ራሴን ለመጠበቅ የሚያስችል እና የአለም አቀፉን ህግ የማይፃረር ነው በማለት ትገልፃለች፡፡ አሜሪካ ይህን የቴህራንን ድርጊት እየተቃወመች ትገኛለች ፡፡

ኢራን አሁን በመካከለገኛው ኢስያ ካሉ ሀገራት አንጻር ግዙፍ የሚሳኤል አንቀሳቃሽ በመሆኗ ከሳውዲ አረቢያ እና እስራኤል ጋር ያላትን ልዩነት በወታደራዊ ፍጥጫ ለመወጣት ያሰበች ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሶሪያ፣ ለየመን እና ለፍልስጤም ህዝቦች የማደርገውን ድጋፍ ማንም ሊያስቖመኝ አይችልም ማለቷ እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመካከለኛው እስያ ቀጠና ላይ ባለው ውጥረት የተነሳ የኢራንን የበላይነት ለመቀልበስ ሲባል ለዘመናት በጠላትነት የሚተያዩት ሳውድ አረቢያ እና እስራኤል በአንድ ግንበር ቆመዋል፡፡ ሳውዲ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በማለት ከእስራኤል ጋር ለማበር ተገዳለች፡፡ 

አሜሪካ ኢራንን በያዝነው ወር በየመን ለሚገኙ የሁቲ አማፂያን ወደ ሳውዲ የተወነጨፈውን ሚሳኤል አቀብላለች በማለት እየከሰሰቻት ሲሆን የመንግስታቱን ድርጅትን ስምምነትም ጥሳለች ትላለች፡፡ ኢራን በአንፃሩ  ለነዚህ ሀይሎች ምንም አይነት መሳሪያ አላቀበልኩም እያለች ትገኛለች፡፡

የሆነው ሆኖ ግን ኢራን በሚሳኤል ማምረት ፕሮግራሟ ላይ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ እያስጠነቀቀች ነው፡፡ የማንንም ማስፈራሪያ እና ማዕቀብ የምንሰማበት ጊዜ አይደለም ሲሉ የኢራን  መከላከያ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ሳላሚ ተናግረዋል ሲሉ ሮይተርስ እና ፕሬስ ቲቪ ዘግበዋል፡፡