በሜክሲኮ በደረሰ የመኪና አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

በሜክሲኮ በደረሰ የመኪና አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።

በምስራቅ ሜክሲኮ ቨራክሩዝ ግዛት በዛሬው ዕለት አንድ የመጓጓዣ መኪና እና የጭነት መኪና ተጋጭተው በተፈጠረ አደጋ የ21 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪም 30 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

የመኪና አደጋው የተከሰተውም ማልትራታ ተብሎ በሚጠራው እና ከባህር ወለል በላይ 2ሺህ ሜትር ከፍታ ባለው ተራራማ ስፍራ ነው ተብሏል።

አደጋው የተፈጠረውም  የአንደኛው መኪና ሾፌር የተሽከርካሪውን ፍሬን መቆጣጠር ተስኖት የመንገዱን አቅጣጫ ስቶ ከሌላኛው መኪና ጋር በመጋጨቱ ነው የተባለው።

ሁለቱ መኪናዎች እርስ በርስ ከተጋጩ በኋላም በእሳት መያያዛቸው ተገልጿል።

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በሜክሲኮ ደቡብ ምዕራብ የምትገኘው ቺያፓስ ግዛት ነዋሪዎች መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

አደጋው የደረሰባቸውም በሜክሲኮ ከተማ የሚገኘውን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጎብኝተው በመመለስ ላይ እያሉ ነው ተብሏል፡፡

አደጋውን ተከትሎም የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በጉዳቱ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝተዋል።

(ምንጭ፡-አልጀዚራ)