ሚያዚያ 02/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ከመሙላቷ በፊት ሱዳንና ግብጽ ለመረጃ ልውውጥ የግድብ ኦፕሬተሮቻቸውን እንዲሰይሙ ጥሪ አቅርባለች።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ለአገራቱ የውሃ ሚኒስትሮች በጻፉት ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ውሃ የፊታችን ሀምሌ እና ነሀሴ ላይ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አገራቱ የግድብ ኦፕሬተሮቻቸውን እንዲሰይሙ ጋብዘዋል።
በደብዳቤ መሰረትም ይህ ግብዣ ለአገራቱ ሊቀርብ የቻለው አስቀድሞ የግድቡን የውሃ አሞላል በተመለከተ በሶስቱ አገራት የገለልተኛ የሳይንቲስቶች ተመራማሪ ቡድን በቀረበውና በተስማሙበት መርሀ ግብር መሰረት መሆኑን ኢፕድ ገልጿል።
በዚህም ሁለተኛው ግድቡን ውሃ የመሙላቱ ስራ ሀምሌ እና ነሀሴ እንደ ውሃው የፍሰት መጠን ታይቶም ግድቡን ውሃ የመሙላቱ ሂደት እስከ መስከረም ሊቀጥል ይችላል ተብሏል።