በመተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የሚሠራ ክልል አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቋመ


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከቀዬቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሠራ ክልል አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ መለሰ በየነ፣ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት እና ሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በመተከል ዞን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተፈናቀሉ ዜጎች አሁን እየተደረገ ካለው ሰብአዊ ድጋፍ ባሻገር በዘላቂነት ለማቋቋም ክልል አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሜቴ መዋቀሩን አቶ መለሰ ተናግረዋል።

ኮሚቴው በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ድጋፍ እንደሚያሰባስብ ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ዜጎችን ካሉበት ችግር ለመታደግ እና በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የገቢ ማሰባሰብ ሥራውን እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

ኮሚቴው በቀጣይ የሚያሳውቃቸውን የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለተፈናቀሉ ዜጎች የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

(ምንጭ ፡- የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)