ህዝብና ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገራዊ ምርጫው ነጻና ተአማኒ እንዲሆን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

መጋቢት 02/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖርቲዎችና ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት የዘንድሮ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻና ተአማኒ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጠየቁ።

በሀገሪቱ አንዱን መጤ፣ ሌላኛውን ቤተኛ የሚያደርጉ የአስተሳሰብና የአመለካከት ዝንፈቶችን በማረም ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን ለማረጋገጥ ታቅዶ መሰራት እንዳለበትም ዋና አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ አሳስበዋል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 17ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ዋና አፈ ጉባኤዋ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፣ በምርጫ ተወዳድሮ  በማሸነፍ  ስልጣን ላይ መውጣትና መምራት የሚቻለው ሀገርና ህዝብ ሲኖር ነው።

ምርጫ የሰለጠነ ህዝብ በሰለጠነ አግባብ ያለምንም ግርግርና ሁከት ይመራኛል የሚለውን ፓርቲ በነጻነት መርጦ ወደ ስልጣን የሚያወጣበት የዘመናዊ ስርአት መገለጫ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብና በክልሉ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመስራት ሀገር  የማሻገር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስገንዘባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።