በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማልማት የ60 ሚሊዮን ዶላር በጀት ጸደቀ

የኢትዮጵያ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አቢይ ኮሚቴ

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት ዐቢይ ኮሚቴ ለ2016 የበጀት ዓመት በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ የሚውል የ60 ሚሊዮን ዶላር በጀት አጸደቀ፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የዐቢይ ኮሚቴው ስብሰባ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ በፕሮጀክቱ ማስተባበሪያና ማስፈጸሚያ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመድረኩ የዐቢይ ኮሚቴው አባል የሆኑ ሚኒስቴሮች እና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የአምስት ክልል የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ በ2015 የበጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ ስራ አፈጻጸም መሰረት የሚጥሉ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶችን የማደራጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን የማሟላት፣ በማህበረሰብ ደረጃ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ አደረጃጀቶችን የማቋቋምና የማጠናከር፣ ለፕሮጀክቱ ባለሙያዎች በፕሮጀክቱ የፋይናንስ፣ የግዥ፣ የአካባቢያዊና የማህበራዊ ደህንነት መርሆችና አሰራሮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መከናወኑ በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡

በፕሮጀክቱ ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ ፈጣን ምላሽ የሚሹ ስራዎችን ለማሳለጥ የዝግጅት ስራዎቹ ጊዜ በመውሰዳቸው በተጠቃሚው ህብረተሰብ እና በፕሮጀክቱ ባለድርሻ አካላት የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውም በውይይቱ እንደ ድክመት ተነስቷል፡፡

በቀጣይ የ2016 በጀት ዓመት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተግባራዊ ለማድረግ ጠንካራ ስራ እንደሚጠበቅ አቅጠጫ የተቀመጠ ሲሆን ኮሚቴው ለፕሮጀክቱ 60 ሚሊዮን ዶላር በጀት ማፅደቁ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም ባንክ መካከል በተደረገ ስምምነት እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ በ300 ሚሊዮን ዶላር በጀት ለአምስት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት መሆኑም በመረጃው ተገልጿል፡፡