ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አደረገ

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ በተሰጠበት ወቅት

ሐምሌ 19/2015 (ዋልታ) የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አመራሮችና ሰራተኞች ለዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አደረጉ፡፡

በዛሬው እለት ከተቋሙ ሰራተኞች የተሰበሰበውን ድጋፍ ለድርጅቱ ያስረከቡት የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ ሐሰን ህፃናት ላይ የሚሰሩ በጎ ተግባራት ነገ ለምንመኛት የበለፀገች ኢትዮጵያ ትልቅ መሰረት በመሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዋልታ አመራሮችና ሰራተኞች የዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅትን ከዚህ ቀደም በጎበኙበት ወቅት ህጻናቱ አልባሳት እና ጫማዎች እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ይህንን ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራው ሁሉ ትውልድን የመገንባትና የማነፅ ተግባር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በቀጣይም ተቋሙ በሁሉም ረገድ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች እናት ዘውዲቱ መሸሻ በበኩላቸው ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ህፃናቱንና አረጋዊያኑን ለመርዳት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘውዲቱ መሸሻ ህፃናትና የቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት ከ30 ዓመታት በላይ ህፃናትን በመንከባከብና በመደገፍ አስተምሮ ለቁም ነገር ማብቃቱም ተመላክቷል፡፡

በቤተልሄም እሸቱ