ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ የክረምት ዝናብ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተገለጸ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ የተወሰኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ተፅዕኖ ውስጥ እንደሚወድቁ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም እንደገለጹት፤ ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ የክረምቱ ዝናብ ተፅዕኖ ሊበረታ ስለሚችል በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
የክረምቱ ዝናብ ተፅዕኖ በኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉ-አባቦራ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች፤ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃምና የባህር ዳር ዙሪያ፤ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በሲዳማ ዞኖች ከዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች መጠናከር ጋር ተያይዞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብለዋል።
ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ የክረምት ዝናብ ተፅዕኖው ሊጀምር እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አህመዲን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በማሳ ላይ ውሃ የመተኛትና ሰብሉን የማበላሸት ተፅዕኖም ሊያደርስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል ፡፡
እንደ ኢፕድ ዘገባ በአንዳንድ ተፋሰሶች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆምም ሁኔታው በአዎንታዊ ጎኑ የወራጅ ውሃ መጠን ስለሚጨምር ለግድቦችና ለውሃ ማቆሪያ ኩሬዎች ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
ዝናቡ በአርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች ስለሚጨምር የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉም መክረዋል።