“የሩሲያ – አፍሪካ አጋርነትና ግንኙነት ጠንካራ ጥልቅ እና ፅኑ በመተማመን እና በበጎ ፈቃደኝነት ላይ መመስረቱ መለያው ነው፡፡” የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሐምሌ 17/2015 (ዋልታ) “የሩሲያ- አፍሪካ አጋርነትና ግንኙነት ጠንካራ ጥልቅ እና ፅኑ በመተማመን እና በበጎ ፈቃደኝነት ላይ መመስረቱ መለያው ነው” ሲሉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገልጸዋል፡፡

በሩሲያዋ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ሐምሌ 20 እና 21 ሁለተኛው የሩሲያ -አፍሪካ የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ፎረም ይካሄዳል፡፡

ፎረሙን አስመልተው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጽሁፍ ስፑትኒክ እንዳስነበበው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን በዋናነት አገሮች እና አህጉራዊ ተቋማት ከሩሲያ ጋር ስለሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ የሰው ኃይል ልማት በዓለም አቀፍ መድረክ ስለሚኖራቸው ትብብር እና መደጋገፍ ሰፊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

የሩሲያ እና አፍሪካ ወዳጃዊ ግንኙነትን አስመልክተው ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት “በሩሲያና በአፍሪካ መካከል ያለው የአጋርነትና ግንኙነት ጠንካራ ጥልቅ እና ፅኑ በመተማመን እና በበጎ ፈቃደኝነት ላይ መመስረቱ መለያው ነው” ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ያለማቋረጥ የአፍሪካዊን ጸረ-ቅኝ ግዛት እና ጭቆና ትግል ከመደገፏም በላይ አገራቸው የአፍሪካ ሀገራትን ሉዓላዊነት እና ነፃ አጋርነት ጥረት ስታግዝ መቆየቷን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ ሁሌም በፅኑ የምንደግፈው ነው፡፡ አፍሪካዊያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መወሰንን ፍትህ እና ህጋዊ መብታቸውን በማስከበር ሂደት ሁሌም ከጎናቸው እንቆማለን ብለዋል፡፡

በውስጣዊ መዋቅሮቻቸው የአመራር ዘዬአቸው፣ የልማት ግቦች እና እነሱን ለማሳካት ስለሚከተሏቸው መንገዶች የራሳችንን ፍላጎት በአፍሪካዊያን ላይ ለመጫን ሞክረን አናውቅም ያሉት ፑቲን ለአፍሪካ አገራት ሉዓላዊነት ያለን ክብር ለባህላቸው እና እሴቶቻቸው የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን እና ከአጋሮች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት በነፃነት እንዲያከናውኑ የሩሲያ አቋም አሁንም ያልተለወጠ መሆኑንም አስረግጠው ገልጸዋል።

ሩሲያ እና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላቸውን ግንኙነት እና ትብብር አስመልክተው እንዳሉት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እና ቡድን 20 አገራትን ጨምሮ የዓለምን እጣ ፈንታ በሚወስኑ መድረኮች ሁሉ አፍሪካዊያን ተገቢ ቦታ እንዲኖራቸው እንዲሁም የዓለም የፋይናንስና የንግድ ተቋማት ጥቅሞቻቸውን በሚያስከብር መልኩ ማሻሻያ እንዲያደርጉ አገራቸው ሁሌም ከጎናቸው እንደምትቆም አስረግጠዋል፡፡

ለዓለም አቀፍ ህግ ቅድሚያ በመስጠት ብሄራዊ ጥቅምን በማክበር የተሟላ የደህንነት እና የተባበሩት መንግስታት የአስተባባሪነት ማዕከላዊ ሚናን በመገንዘብ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ስርዓት ለመቅረጽ በጋራ ለመስራት አብረን ቆመናል ሲሉ የአፍሪካ – ሩሲያን ፎረም አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

አፍሪካ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከላቲን አሜሪካ ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ተገቢ ቦታዋን እንደምትይዝ እና በመጨረሻም ከቅኝ ግዛት እና ከዘመናዊው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መራር ትሩፋት ነፃ እንደምትወጣ ቅንጣት ጥርጥር የለኝም ሲሉ ስለአፍሪካ መጻኢ ጊዜ በእርግጠኝነት የገለፁት ፑቲን በዚህም ጥረቷ አገራቸው የዓለም ስርዓት እንዲሻሻል እና አፍሪካም በዓለም መድረክ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጭነት ሚና እንዲኖራት እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡

ፎረሙ ሁሉን አቀፍ መግለጫን፣ በርካታ የጋራ መግለጫዎችን እንደሚወጡበትና ለ2026 የሩሲያ – አፍሪካ አጋርነት ፎረም የድርጊት መርሃ ግብርን እንደሚያጸድቅ ሲጠበቅ ርዕሰ መንግስታት ርዕሰ ብሔሮች ኢንተረፐረነሮች ተመራማሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች በጉባኤው እንደሚሳተፉ በፕሬዝዳንቱ ፅሁፍ ተጠቅሷል፡፡