የኖርድ ስትሪም የጋዝ መስመር ጥቃት በዩክሬናዊ ኮማንደር አስተባባሪነት መፈጸሙ ተገለጸ

ሕዳር 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ከሩሲያ ወደ አውሮፓ በተዘረጋ ኖርድ ስትሪም የጋዝ መስመር ላይ የደረሰው ጥቃት በዩክሬናዊ የጦር ኮማንደር አስተባባሪነት እንደተፈጸመ ዋሽንግተን ፖስትና የጀርመኑ ዴር ሽፔግል ጋዜጦች በጋራ ባካሄዱት ምርመራ ማረጋገጣቸው ተገለጸ፡፡

ኖርድ ስትሪም አንድና ሁለት በተባሉ የጋዝ መስመሮች ላይ ጥቃቱን ማን ፈጸመው የሚለው ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ መቆየቱንና አሜሪካ፣ ሩሲያና ዩክሬን ቀዳሚ ተጠርጣሪ አገራት ተደርገው ሲወሰዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ጋዜጦች በኖርድ ስትሪም ላይ ጥቃት ያደረሰውን አካል ለማወቅ ባደረጉት ምርመራ ሮማን ቼርቪኒስኪ የተባለ የ48 ዓመት የቀድሞ የዩክሬን የልዩ ዘመቻ አባል እንዳስተባበረው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በዩክሬንና በሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ የመረጃ ምንጮች እንዲሁም ስለ ጥቃቱ እውቀቱ ያላቸው ሰዎች መረጃ ሰጥተውናል ብለዋል፡፡

ሰውዬው ጥቃቱን ለመፈጸም ለተመለመሉ ስድስት ሰዎች የሚያስፈልጉ እንደ ጀልባ፣ ሃሰተኛ መታወቂዎችንና ፈንጅዎችን በጥልቁ ባህር ለማጥመድ የሚያስፈልጉ የጠለቃ መሳሪያዎችን በማሰባሰብ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ለማወቅ እንደቻሉ ፍራንስ 24 በዘገባው አመላክቷል፡፡

ሰውዬው በጠበቃው በኩል በሰጠው ማስተባበያ በጥቃቱ እጁ እንደሌለበት፣ መረጃው መሰረተ ቢስ ክስና የሩሲያ ፕሮፖጋንዳ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በተለያዩ ጊዜያት በሰጡት መግለጫ ዩክሬን በጥቃቱ እንጇ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ስለ ጥቃቱ ዕቅድ መረጃ እንዳልነበራቸው ምርመራውን ያደረጉት ጋዜጦች ጠቁሟል፡፡

ቸርቪኒስኪ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ያላግባብ በመጠቀም ወንጀል ተከሶ በኪዬቭ ፍርድ ቤት በክርክር ላይ መሆኑን መረጃው ጨምሮ ገልጿል፡፡

በዴንማርክ የውሃ ክልል በሆነው ማዕከላዊ ባልቲክ ባህር አካባቢ በደረሰው ፍንዳታ ከሩሲያ ወደ አውሮፓ ከተዘረጉት አራት የጋዝ መስመሮች በሶስቱ ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡