የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናወኑ

ሐምሌ 2፣ 2013 (ዋልታ) – የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡

“ኮቪድ-19ን እየተከላከልን ኢትዮጵያን እናልብሳት!” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የጤና ሴክተር  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት  ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

በዛሬው ዕለት 10ሺ ችግኞች መተከሉን የገለፁት ዶክተር ሊያ÷ በያዝነዉ ክረምት ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች 810 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው÷ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እንደ ሀገር የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ ግብን ማሳካት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተተከሉት ችግኞችን በመከታተል ተገቢውን ክብካቤ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ በየቦታው ችግኞችን በሚተክልበት ወቅት ከኮሮና ቫይረስ እራሱን ለመከላከል ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማድረግ እንዳለባቸው ዶክተር ሊያ ማሳሰባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡