ዶናልድ ትራምፕ አዲስ ክስ ተመሰረተባቸው

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ሐምሌ 21/2015 (ዋልታ) የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደህንነት ካሜራ የተቀረጸን መረጃ እንዲያጠፋ በአንድ ሰራተኛ ላይ ጫና አድርገዋል በሚል አዲስ መረጃ የማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው ማራላጎ በተሰኘው ቤታቸው ከተገኙት የመንግስት ሚስጥራዊ ዶሴዎች ጋር በተያያዘ መንግስት እያደረገ ያለውን ምርመራ ለማደናቀፍ በማሰብ የተቀረጸን የደህንነት ካሜራ መረጃ ከሰርቨር ለማስጠፋት ሰራተኛው ላይ ጫና አድርገዋል ነው የተባለው፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንቱ እንዲጠፋ የፈለጉት የደህንነት ካሜራ ምስል በህገወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤቱ የነበሩ መረጃዎች ወደ ሌላ ቦታ ሲወሰዱ እንደሚያሳይ አቃቤ ህግ ገልጿል፡፡

የማራላጎ ሰራተኛ የሆነ ሌላ ሰራተኛም ከፕሬዝዳንቱ መመሪያ ተቀብሎ ሌላን የአይ.ቲ ሰራተኛ መረጃውን እንዲያጠፋ አድርጓል በሚል ክስ እንደቀረበበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት በዚሁ መኖሪያ ቤታቸው ከፍተኛ የመንግስት ሚስጥራዊ ዶሴዎችን አከማችተው በመገኘታቸው በርካታ ክሶች ቀርበውባቸው በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአሜሪካ መንግስት ሚስጥራዊ መረጃዎችና ዶሴዎች በህግ ከተደነገገው ቦታ ውጭ መጓጓዝም ይሁን ማከማቸት ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡