ፌዴሬሽኑ በአወዛጋቢው የማራቶን ውጤት ላይ ምርመራ እንደሚያከናውን አስታወቀ

ሚያዝያ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአወዛጋቢው የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ውጤት ላይ ምርመራ እንደሚያከናውን አስታወቀ።

ባለፈው እሁድ በተደረገው የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ሦስት አፍሪካዊያን አትሌቶች ሆን ብለው ሄ ጂ የተባለው ቻይናዊ አትሌት እንዲያሸንፍ ማድረጋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ እንግዳ ከአዲስ ዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዕለቱ ውድድር ላይ የተሳተፈው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጀደኔ ኃይሉ ከፌዴሬሽኑ እውቅና ውጭ ወደ ውድድሩ ስፍራ ማቅናቱን ገልጸው ያደረገውን ተግባር እንደሚያጣራ አስታውቀዋል።

የውድድሩ አዘጋጆች በምን መስፈርት ተወዳዳሪውን እንዳሳተፉት ፌዴሬሽኑ እንደማያውቅ አመልክተዋል። አትሌቱ ወደ ሀገር ሲመለስ ፌዴሬሽኑ ስለሁኔታው እንደሚያነጋግርም አንስተዋል።

በቤይጂንግ ግማሽ ማራቶን ላይ የተሳተፉት ኬኒያዊያኑ ሮበርት ኬተር፣ ዊሊ ምናንጋት እና ኢትዮጵያዊው ደጀኔ ኃይሉ ከስፖርታዊ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ሆን ብለው ሌላ ተወዳዳሪ እንዲያሸንፍ ፍጥነታቸውን በመቀነስ እንዲሁም በማበረታታት እንዲያሸንፍ ማድረጋቸው በተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

በሐብታሙ ገደቤ