የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት እንደሚደረጉ ተገለፀ

ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ጨምሮ በአገሪቱ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት እንደሚደረጉ መንግሥት ገለፀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ ለተለያዩ አኅጉራት አምባሳደሮች በአዲስ አበባ በሰጡት ማብራሪያ እንዲሁም ከሰሞኑ ከቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ ሁሉን አካታች ውይይት እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል፡፡
ውይይቶቹ በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው አገራዊ የምክከር ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅና ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ ሆኖ በመደራጀት ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ በሚላቸው ሐሳቦች ላይ በሚቀርፃቸው አጀንዳዎች እየተመራ እንደሚሄድ ተገልጿል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በማብራሪያቸው ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እየፈቱ የሚሄዱበትና ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ጉዳዮች እየተነሱ ምክክር የሚደረግበት መድረክ እንደሚሆን መንግሥት እንደሚጠብቅም ጠቁመዋል፡፡